የዳዉሮ ባህልና ቋንቋ ዕድገት ከየት ወደት ?

ባህልና ቱሪዝምየኢትዮጵያ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሀገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህል፣ታሪክ፣ቋንቋና ቅርስ ተጠንቶና ለምቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ፤ ለህብረተሰቡ ዕድገትና ልማት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላይ እንዲውል ህገመንግስታዊ ዕውቅና ተሰጥቶት የህግ ከለላ ተደርገውላቸዋል፡፡ ከነዚህ መካከል የዳውሮ ብሄረሰብ ባህል፣ታሪክና ቋንቋ አንዱ ነው፡፡የብሄረሰባችን ባህል ሰፊ ባህር ነው፡፡ሁሉንም ለመዘርዘር እራሱን የቻለ ዝግጅትና ህትመት ስለሚጠይቅ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በባህል ዘርፍ የታዩ ለውጦች በርካታ ሲሆኑ አንኳር የሆኑትን እንደሚከተለው መተንተን ይቻላል፡፡

 • ዳውሮ ብሄረሰብ ቱባ ባህላዊ፣ትውፊታዊና ስነ-ጥበባዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ የዳውሮ ባህል ኪነት ባንድ ተቋቁመውና ተደራጅተው የብሄረሰቡ ባህል በሌሎች መጤ ባህሎች እንዳይበረዝና ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ የበኩሉን ሚና ከመጫወቱም በላይ የብሄሩን ገጽታ ለዓለም ህብረተሰብ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል፡፡
 •  በዓለም በርዝመቱ የመጀመሪያ የሚሆነው የዲንካ ባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያችን ተጠንቶ በመጽሀፍ እንዲታተም ተደርገዋል፡፡
 •  እየጠፉና እየቀሩ የሄዱ የዳውሮ ብሄረሰብ ባህላዊ አልባሳት ማዳ ማሻ፣ዱንጉዛ ሀዲያና ዳዋሊያ ዳንጩዋ፣ዋሩዋ ቡሉኩዋ… ጥንታዊነቱና የጥለት አጣጣል ዲዛይኑ ሳይለወጥ ለምቶ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላይ በመዋል በሸማ ሥራ የዕደ-ጥበብ ዘርፍ ለተሰማሩ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የበኩሉን ሚና ተጫውተዋል፡፡
 • የዳውሮ ብሄረሰብ ባህላዊ የቆዳ ምንጣፍ (ማንቻላ) ተጠንቶ እንዲታወቅ ተደርገው የገበያ ትስስር እየተፈጠረለት ይገኛል፡፡  
 • የዳውሮ ብሄረሰብ የባህል፣የታሪክ፣የቋንቋና የስነ-ጥበብ ፌስቲቫልና ቶኪ-ቤዓ (የዘመን መለወጫ በዓል) ተጠንቶ በህብረተሰቡ ዘንድ በየዓመቱ እየተከበረ ሲሆን በአገር ብሎም በአለም ደረጃ በማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት እንዲመዘገብ ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡
 • ታሪካዊ የዳውሮ ንጉስ ካዎ ሀላላ የድንጋይ ካቦች(Kati Halaala Keela)ተጠንቶ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በብሄራዊ ቅርስነት ተመዝግበው እውቅና የተሰጠው ሲሆን በዓለም ቅርስነት በዩኒስኮ እንዲመዘገብ መስፈርቶቹን ያሟላ ጥናት በባለሙያዎች እየተካሄደ ይገኛል፡፡
 • የዳውሮ ህዝብ ታሪክ በመጽሀፍ በመታተም እንዲሰራጭ ተደርገዋል፤የዳውሮ ብሄረሰብ የባህል፣የታሪክ፣የቋንቋና የቅርስ ጥናትና ምርምር ማዕከል (ዱቡሻ) በህብረተሰባችን የነቃ ተሳትፎ ተገንብቷል፡፡ የብሄረሰባችን የማንነት መገለጫና የታሪክ አሻራ የሆኑ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችና የወግና ባህል ዕቃዎች በሙዚዬም ተሰበሰስበው ለጎብኚዎችና ለተመራማሪዎች አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ በዞናችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ቋሚ ቅርሶች ተለይተው በመመዝገብ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡
 • ኢትዮጵያ በቋንቋ ዘርፍ ህብረ-ብሔራዊ ሀገር ብትሆንም በጣት ከሚቆጠሩ ቋንቋዎች ውጭ ሌሎቹ ተቀብረውና ማንነታቸው ሳይታወቅ እስከ 1983 ዓ.ም መቆየታቸው ታሪክ የማይዘነጋው ሀቅ ነው፡፡ የዳውሮኛ ቋንቋም ተቀብሮ እንዲጠፋ ብይን ከተሰጡባቸው ቋንቋዎች አንዱ ሲሆን የ1983 ዓ.ም ደርግ መንግስት ግብዓተ መሬቱ ሲበስርና የኢፌዲሪ መንግስት ሀገሪቱን መቆጣጠር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያዘቀዘቀችው ፀሀይ ዳግም በመብራት ከህጎች ሁሉ የበላይ በሆነው ህገ-መንግስቱ ጭምር ሙሉ ዋስትና በመስጠቱ ቋንቋው በተቃራኒው  በፍጥነት መልማት የጀመረበት መሰረት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በ1987 ዓ.ም ጀምሮ በላቲን የአፃፃፍ ስልት በ1ኛ ደረጃ መሰጠት የጀመረው የዳውሮኛ ቋንቋ፣ በ1989 ዓ.ም ጀምሮ በመለስተኛ ደረጃዎች መሰጠት ተጀምረዋል፡፡
 • ከ1987-1992 ዓ.ም ድረስ በዳ.ጋ.ጎ፣ከ1992-1993 ዓ.ም ከወ.ጋ.ጎ.ዳ ጋር ተዳብለው ሲሰጥ የቆየው የዳውሮኛ ቋንቋ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ራሱን የቻለ በመሆን የመልማት ዕድሉ ይበልጥ ምቹ ሆኖለታል፡፡
 • በ2003 ዓ.ም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መሰጠት የተጀመረው የዳውሮኛ ቋንቋ ከነሙሉ  ማስተማሪያ መጽሀፍት ቋንቋው ተሟልተውለት እንደ አንድ ትምህርት ሆኖ በመሰናዶ ደረጃ መሰጠት ተጀምረዋል፡፡ በተጨማሪም የቋንቋውን ዕድገት የሚያሳልጡ በርካታ አጋዥ መጽሀፍት ባለፉት 26 ዓመታት ተጽፈውና ታትመው በጥቅም ላይ ውሏል፡፡
 •  በላቲን የአፃፃፍ ሥልት ፊደል የተቀረፀለት ቋንቋው በውስጡ የሚገኙ ተነባቢዎችና አናባቢዎች ተለይተው መልክ የተያዘበት ሲሆን በቋንቋው የተዘጋጀ አሀዳዊ መዝገበ-ቃላት በመታተም ለትምህርት ቤቶች ተሰራጭተው ተማሪዎች፣መምህራንና ተመራማሪዎች በቋንቋው እንዲጠቀሙ አድርገውታል፡፡
 • የዳውሮኛ ቃላት እንዳይሞቱና አገልግሎቱ እንዳይስተጎጉል ሲባል ቃላቱን መሰረት ያደረገ የስነዳ ሥራ በዩኒቨረስቲ ምሁራን ተሰርተው በርካታ ቃላት እንዲሰነዱ ተደርገዋል፡፡ (Language Documentation Based Lexical Study of the Earlier Dawuro Kingdom-Dr.Dawit Bekele 2016-unpublished dissertation paper) በሚል ርዕስ የጻፈው በዋናነት ማንሳት ይቻላል፡፡
 •  በተጨማሪም ከ6 በላይ ታላላቅ ጥናታዊ ጹሁፎች በቋንቋው ላይ በከፍተኛ ባለሙያዎች የተደረጉ ሲሆን ይህም ቋንቋው ትልቅ መሰረት እንዲኖረው ያደረገ ነው፡፡

      ለምሳሌ፡-

 1. Aspects of Dawuro Phonology:-(Tariku Negese  2010)-Ma Thesis
 2. Verb Complements of Dawuro:-Alebachew Biadgie (2010)-Ma thesis
 3. Some Aspects of the phonology and Morphology of Dawuro:-(Dr. Hirut W/Mariam 2007:71-121)
 4.  Notes on the North Ometo Dialects :Mutual intelligibility tests and structural variations-(Dr. Hirut W/Mariam 2004:79-112)
 5. Problems of WOGAGODDA Orthography-Dr. Hirut W/Mariam (1998:3-4)
 6. Ometo Verb Derivations: The Case of Basketo, Male, Koreto and Kullo :- (Dr. Hirut W/Mariam 1994፡121-29)
 7. Kulo Verb Morphology-(Dr. Hirut W/Mariam፡1998)
 8. Attitudes of Students,Teachers,Parents and Education Bureau Officials Towards Dawurogna as a medium of instruction in primary schools in Dawuro Zone Dr. Mitiku Mekuria (2005) በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ (All research papers are available at Dawuro culture center’s Library.)
 • ቋንቋው በሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ እንዲታወቅና ለተለያዩ ዓላማ መጠቀም እንዲችሉ የዳውሮኛ-አማርኛ-እንግሊዘኛ መዝገበ-ቃላት ተዘጋጅተው መታተሙ ትልቅ ዜና ነው፡፡
 • የቋንቋውን ይዘት በጥልቀት መመራመር እንዲያስችል የዳውሮኛ ሰዋሰው መጽሀፍ ተዘጋጅተው ለትምህርት ቤቶችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሰራጭተዋል፡፡
 • በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነገሩ በርካታ ትርጉም ያላቸው ስነ-ቃሎች እየተሰበሰቡ ሲሆን ከዚህም መካከል የመጀመሪያ ክፍል የሆነው የዳውሮኛ ምሳሌያዊ ንግግሮች ታትመው ለ መለስተኛ እና ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተሰራጭተዋል፡፡
 • በልቦለድ እና በግጥም መልክ የብሄረሰቡን ወግ፣ባህል የሚያሳዩ መጽሀፍት በብሄረሰቡ ደራሲያን ተደርሰው ለንባብ በቅተዋል፡፡
 • የኪነ-ጥበብ ዘርፉን ለማሳደግና መልካም ገጽታ ከመገንባት ረገድ አዳዲስ ወጣቶች ወደ ዘርፉ በመምጣት ለሥነ-ጥበብ ዘርፍ ዕድገቱ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
 • የዳውሮ ህዝብ በራሱ ቋንቋ እንዲወያይበት፣እንዲጠያይቅና እርስ በርስ ልምድ እንዲለዋወጥ የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ዋካ ቅርንጫፍ አገልግሎት እየተሰጠበት መሆኑ፣
 • በ2003 ዓ.ም አካባቢ ለአንደኛ ደረጃ መምህራን በአርባምንጭ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መሰጠት የተጀመረው ዳውሮኛ በ2007ዓ.ም የራሱን የትምህርት ክፍል በመክፈት እነሆ በ2009 ዓ.ም መጠናቀቂያ ላይ በቀንና በክረምት መርሀ ግብር በርካታ መምህራን በዘርፉ ሰልጥነው መመረቃቸው ሲታይ የቋንቋን ዕድገት ከፍታ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
 • በተጨማርም የዳዉሮኛ ቋንቋ በወላይታ ዩኒቨርስቲ ዳዉሮ-ታርጫ ካምፓስ በድግሪ ፕሮግራም ለማስጀመር የካሪኩለም ቀረጻ ሥራ አልቆ መምህራን የተቀጠረ ስሆን በ2011 ዓ.ም መረሀ ግብር መደበኛ ት/ት በድግሪ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
 • በአጠቃላይ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ዳውሮኛ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ዕድገቱን በማፋጠን በአህኑ ወቅት ከኮሌጅ አልፎ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ታርጫ ካምፓስ አንድ የትምህርት ክፍል በመሆን ተከፍተው በ2011ዓ.ም ተማሪዎቹን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀው በዘርፉ የተመረቁትን መምህራን መቅጠሩ ሲታይ ደስታችንን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡

ሆኖም የዳውሮ ባህልና ቋንቋ ከዚህ አልፎ ህገመንግስቱ የሰጠውን መብት ሙሉ በሙሉ መተግበር እንዲችል ያልተሰሩ በርካታ የቤት ሥራዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ዋናዋናዎቹ፡-

 • ቋንቋው የሥራና የጽሁፍ ቋንቋ እንዲሆን በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መስራት፣
 • በቋንቋው የተጻፉ መጽሀፍት በሰፊው ታትመው ለንባብ እንዲበቁ ማድረግ፣
 • በየወቅቱ ቋንቋው የደረሰበትን ደረጃ የሚመጥን ዕቀዳ በማዘጋጀት ለባለድርሻ አካላት ማቅረብ፤
 • ባህል፣ታሪክና ቅርስ አሁን ካለበት ደረጃ ወደ ከፍታ ማውጣት፣ለዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ማድረግ፣
 • በባህል ልማት ላይ የባለድርሻዎች ግንዛቤ ማሳደግ ዋናዋና ተግባራት ሲሆኑ በዚህ ዙሪያ የባለድርሻዎች ያልታከተ ጥረት አሁንም የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

                      በዳውሮ ዞን ባ/ቱ/መ/ኮ/ጉ/መምሪያ በቋንቋና ስነጥበብ  በባህል፣ታሪክና ቅርስ ዋና የሥራ ቡድን በጋራ የተዘጋጀ